የአሰራር መመሪያ እና ማቋቋሚያ ደንብ እንዲሁም የሰላም ሰራዊት ስነ-ምግባር ስልጠና
የሰላም ሰራዊቱ ከሰላም ወዳዱ ህዝብ እና ከጸጥታ አካላት ጋር በቅንጅት በመስራቱ የሰላም አየር መተንፈስ ተችሏል ሲል የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ጽህፈት ቤት ገለጸ።
ታህሳስ 15/2017 ዓ.ም (አዲስ አበባ)
********
ጽህፈት ቤቱ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሰላም ሰራዊት አደረጃጀት የአሰራር መመሪያ እና ማቋቋሚያ ደንብ እንዲሁም የሰላም ሰራዊት ስነ-ምግባርን አስመልክቶም ከ600 በላይ ተሳታፊዎች በተገኙበት የአቅም ማጎልበቻ ስልጠና ሰጥቷል።
በስልጠና መድረኩም የአዲስ አበባ ከተማ የሰላምና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ሚደቅሳ ከበደ ፣ የአዲስ አበባ ከተማ የሰላምና ጸጥታ ቢሮ አማካሪ ሀጂ ኤልያስ መሀመድ እና የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ሰላምና ጸጥታ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፋኖስ ደቻሳ ተገኝተዋል።
የስልጠና መድረኩ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ እና በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ በየብሎኩ የሚገኙ የሰላም ሰራዊት መሪዎችን ያሳተፈ እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን የሁለቱም ክፍለ ከተሞች የወረዳ አመራሮች፣ የሰላም ሰራዊት አባላት እና ጥሪ የተደረገላቸው አካላትም ተሳትፈዋል።
ሰላም ሰራዊት ባለበት ጥፋት እና ተንኮል የሚያስቡ አካላት ነጻነት የላቸውም ያሉት የአዲስ አበባ ከተማ የሰላምና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ሚደቅሳ ከበደ ናቸው።
ከተማችን በርካታ አለም አቀፍ ኮንፍረንሶችን ታካሂዳለች የተለያዩ በዓላትም ይከበራሉ እነዚህን በኣላት እና ኮንፍረንሶች ካለምንም የሰላም እንከን ለማሳለፍም ካለ ሀይማኖት ልዩነት እና ካለ ቋንቋ ልዩነት ልንሰራ ይገባልም ብለዋል አቶ ሚደቅሳ።
ወንጀልን ለመከላከል እና ሰላምን በማስፈን ሂደት ላይ የሰላም ሰራዊቱን በማሰልጠን እና በማሰማራት የተሰራው ስራ ውጤታማ ነበር ያሉት ደግሞ የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ሰላምና ጸጥታ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ታዬ ሽፈራው ናቸው።
ይህ ስልጠናም የሰላም ሰራዊት መሪዎች ሰልጥነው በስራቸው የሚገኙ አባላትንም በማንቃት የአካባቢያቸውን ሰላም አጠናክረው እንዲያስቀጥሉ ማስቻልን ታሳቢ ያደረገም ነው ሲሉም ኃላፊው አክለው ገልጸዋል።
ህዝባችን በሰላም ሰራዊት ተደራጅቶ ከሰላም ወዳዱ ህዝብ እና ከጸጥታ አካላት ጋር በቅንጅት በመስራቱ የሰላም አየር መተንፈስ ተችሏል ሲሉም አቶ ታዬ ለሰላም ሰራዊቱ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
በስልጠናውም ሰፋ ያለ ሰነድ የቀረበ ሲሆን የደንቡ መቋቋም አስፈላጊነት፣ የሰላም ሰራዊት ተግባርና ኃላፊነት፣ ልዩ ልዩ ድንጋጌዎች፣ ስነ-ምግባር ቀረጻ እና የዲሲፕሊን እርምጃ አወሳሰድ እና ሌሎችም ከሰላም ማስከበር ጋር ተያይዞ መከናወን ያለባቸው ጉዳዮች ላይ ስልጠና ተሰጥቶ ውይይት ማድረግ ተችሏል።
ይህ ስልጠና የንድፈ ሀሳብ ስልጠና ሲሆን በቀጣይም ከነገ ጀምሮ ለ 3 ተከታታይ ቀናት የመስክ ስልጠና ይሰጣልም ተብሏል በመድረኩ።
ዘገባው ፡~ የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት ነው