የ2017 ዓ/ም የጥምቀት በዓል የፀጥታ ሁኔታ ቅ...

image description
- recent news   

የ2017 ዓ/ም የጥምቀት በዓል የፀጥታ ሁኔታ ቅድመ ዝግጅት

የዘንድሮ የጥምቀት በዓል አከባበር ያለምንም የጸጥታ ችግር እንዲከበር  በዘመናዊ ቴክኖሎጂና በድሮን የተደገፈ የፀጥታና የደህንነት ቁጥጥር ይደረጋል።

* ክብርት ወ/ሮ ሊዲያ  ግርማ የአዲስ አበባ ከተማ  ሰላምና ፀጥታ  አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ 

         ጥር  03 / 2017 ዓ.ም (አዲስ አበባ)

                        ****
የ2017 ዓ/ም የጥምቀት በዓል የፀጥታ ሁኔታ ቅድመ ዝግጅትን በማስመልከት የአዲስ አበባ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ እና የደንብ ማስከበር ባለስልጣን ከማዕከል እስከ ወረዳ ካሉ የጸጥታ  አመራሮች ጋር ውይይት አድርገዋል።

 የአዲስ አበባ ከተማ  ሰላምና ፀጥታ  አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ክብርት ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ የመክፈቻ ንግግር ሲያደርጉ ከተማችን አዲስ አበባ ትላልቅ ህዝባዊና ሃይማኖታዊ የአደባባይ በዓላት የሚከበሩባትና የአፍሪካ ሕብረት መቀመጫ፣ ትላልቅ  ዓለማቀፍና አህጉር አቀፍ ጉባኤዎች የሚስተናገዱባት እንደመሆኗ መጠን፣ሰላምና ደህንነቷ የተጠበቀ እንዲሆን ቢሮው በዋናነት የፀጥታ አካላትን በማስተባበርና በማቀናጀት እየሰራ ይገኛል ብለዋል። በዚህም አንጸባራቂ ውጤቶች ተገኝቷል። የተገኘው ውጤት ባለቤቱ መላው የከተማችን ህዝብና በተለያየ ደረጃ የሚገኙ የጸጥታ መዋቅር እንደሆነ በመግቢያ ንግግራቸው አንስተዋል።

በመሆኑም ልክ እንደከዚህ ቀደሙ ከፊታች የሚከበረውን የከተራና የጥምቀት በዓል ፍፁም ሰላማዊ በሆነ መልኩ  እንዲጠናቀቅ የቅድመ ዝግጅት ስራ እየተሰራ ይገኛል ብሏል።

ክብርት ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ አክለውም የዘንድሮ የጥምቀት በዓል ልዩ የሚያደርገው በዘመናዊ ቴክኖሎጂና በድሮን የተደገፈ የፀጥታ ጥበቃ እንደሚካሄድ ጠቅሰው፣ ህዝቡ የሰላም ባለቤት ሆኖ የከተማዋንና የአከባቢውን ሰላም በመጠበቅ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያደርግ እንዲሁም  የሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ እና  የደንብ ማስከበር ባለሥልጣን በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች ሚናቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።

በውይይቱም የጥምቀት በዓል የፀጥታና የደህንነት ማስፈፀሚያ ሰነድ  ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል። በሰነዱም የ2016 ዓ.ም የጥምቀት በዓል አከባበር ተሞክሮ፣ የዓለማቀፍ፣ አህጉር አቀፍና አገር አቀፍ የሰላምና የደህንነት ነባራዊ ሁኔታዎችን በመዳሰስ ለከተማችን የሚመጥን የፀጥታ ተቋማት አቅምና ዝግጁነት አስፈላጊ መሆኑ ተጠቅሷል።

የአዲስ አበባ ከተማ የደንብ ማስከበር ባለስልጣን ዋና ስራ ስኪያጅ ሻለቃ ዘርይሁን ተፈራ  በዚህ ወቅት እንደተናገሩት የ2017 ዓ.ም የጥምቀት በዓል በሰላም እንዲከበር የፀጥታ አመራሮች ትኩረት ሰጥተው በዓሉ ፍፁም ሰላማዊ በሆነ መልኩ እንዲከበርና ህዝቡ በሰላም ወጥቶ እንዲገባ መስራት አለባቸው ሲሉ ገልጸዋል።

ውይይቱን የመሩት  የቢሮ ኃላፊ ክብርት ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ  በውይይቱ ማጠቃለያ ላይ በሰጡት አቅጣጫ አመራሩ ከዛሬ ጀምሮ በሺፍት በመግባት የታቦት ማደርያ ቦታ ፍፁም ከስጋት የፀዳና የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዳይኖሩበት ማድረግ፣ የሽብር ሀይሎች እንቅስቃሴ ከጥምር የፀጥታ አካላት ጋር በመሆን መቆጣጠር፣ የፅንፈኝነት ይዘት ያላቸውን መልዕክቶች የመከታተልና የመፈተሽ ስራዎችን ማጠናከር, በአሉን በማስታከክ የሚፈጸሙ ህገ ወጥ ግንባታዎች መከታተል, የለሙ የኮሪደር ልማት ስራዎች በንቃት መጠበቅ እና በየደረጃው ፈጣንና ቀልጣፋ የመረጃ ቅብብሎሽ ሊኖር ይገባል ብለዋል።

በመድረኩ ላይ  የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ሀላፊ ክብርት ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ፣ የደንብ ማስከበር ባለስልጣን ዋና ራ አስኪያጅ  ሻለቃ ዘሪሁን ተፈራን ጨምሮ ሌሎቹም በየደረጃው የሚገኙ የሁለቱም ተቋማት  ኃላፊዎች ተገኝተዋል።