



የህግ የበላይነትና የንግድ ቁጥጥር ንዑስ ኮሚቴው በ90 ቀናት እቅድ::
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የህግ የበላይነትና የንግድ ቁጥጥር ንዑስ ኮሚቴው በ90 ቀናት እቅድ አተገባበር ዙሪያ ውይይት አደረገ።
ሰኔ 12/2017 ዓ.ም (አአሰፀአቢሮ)
*******
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የህግ የበላይነትና የንግድ ቁጥጥር ንዑስ ኮሚቴው በ90 ቀናት እቅድ አተገባበር ዙሪያ ውይይት አድርጓል።
የእቅዱ ዝርዝር በቢሮው የኦፕሬሽን ዘርፍ ምክትል ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ደንድር ቀርቦ ሰፊ ውይይት ተደርጎበታል።
የአዲስ አበባ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ ክብርት ወይዘሮ ሊዲያ ግርማ እንዳሉት የንግድ ቁጥጥርና የህግ ማስከበር ግብረ-ኃይል በቅንጅት በመሰራቱ ባለፉት ወራት አመርቂ ውጤት ማስመዝገቡን ጠቅሰው በዘጠና ቀናት እቅዳችንም ህገወጥ የዋጋ ጭማሪን፣ ኮንትሮባንድን በመከላከል የኑሮ ውድነትን በማረጋጋት ግብረ-ኃይሉ በተቆጠረና በተጨበጠ አግባብ መስራት አለበት። የግብይት ስርዓቱን ህጋዊነት በማረጋገጥ በመናበብ እንሰራለን ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል።
ቢሮ ኃላፊዋ አክለውም የንግድ ቁጥጥር ስርዓቱን በማጠናከር ፣ አነስተኛ ወንጀሎችን ቀድሞ በመከላከል፣ ሀገራዊና ዓለማቀፋዊ ስብሰባዎችን እንዲሁም ብሔራዊና ኃይማኖታዊ በዓላትን ሰላማዊ ማድረግ የዚህ ንፁስ ኮሚቴ ዋነኛ ተግባር የእቅዳችን ቁልፍ ግብ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
በአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮምሽነር ጌቱ አርጋው እንዳሉት ዓለም አቀፍ የፀጥታ ችግሮችን መነሻ በማድረግ የሚፈፀሙ የኢኮኖሚ አሻጥሮችን ቀድመን በመከላከል፣ የፀጥታ ስራችንን በማጠናከር፣ የመንግስትን ገቢ ለማስቀረት የሚምክሩትን አካላት በመቆጣጠር በዘጠና ቀናት እቅድ አፈጻጸም ተቋማዊ ኃላፊነታችን በአግባቡ ልንወጣ ይገባል ብለዋል።
ኮምሽነር ጌቱ ጨምረው እንዳሉት ንዑስ ኮሚቴው በተናበበ አሰራር ህግን በማስከበር ሰላምንና ልማትን በንቃት መጠበቅ አለብን ሲሉ ተናግረዋል።
በቀጣይ የስራ አቅጣጫ ከ4800 በላይ ህገወጥ ነጋዴዎችን ወደ ህጋዊ ማቀፍ በማምጣት እንደሚገባ ተገልጿ።
እስከ ምሽቱ 4 ሰዓት የኮሚቴው አካላት በሽፍት የተጠናከረ ቁጥጥርና ክትትል ማስተካከያ በማድረግ የንግድ ስርዓቱን አገልግሎት ማሻሻል ይገባል ተብሏል።
በተጨማሪም በመጋዘኖች፣ በኬላዎች በነዳጅ ማድያዎችና በፍጆታ ሸቀጥ አቅራቢዎች እንዲሁም አምራቾች አቅርቦትና ስርጭትና ተመጣጣኝ ዋጋ ላይ ጥብቅ ቁጥጥር እንደሚደረግ በክብርት ቢሮ ኃላፊ አቅጣጫ ተቀምጧል።
በዕለቱ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ ክብርት ወይዘሮ ሊዲያ ግርማ፣ በአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮምሽነር ጌቱ አርጋው፣ የአዲስ አበባ ከተማ ደንብ ማስከበር ባለስልጠን ዋና ስራ አስኪያጅ ሻለቃ ዘሪሁን ተፈራን ጨምሮ የንዑስ ኮሚቲው ምክትል ቢሮ ኃላፊዎች፣ የከተማዋ የፖሊስ አዛዦችና የክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ኃላፊዎች እንዲሁም ሌሎችም አመራሮች ተገኝተዋል።