ከፊታችን በሚከበሩ በመስቀል ዳመራና ኢሬቻ በዓላ...

image description
image description
image description
image description
image description
image description
- recent news   

ከፊታችን በሚከበሩ በመስቀል ዳመራና ኢሬቻ በዓላት ላይ ውይይት ተካሄደ።

የአዲስ አበባከተማ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ከ ህብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን ጋር በመተባበር ቁጥራቸው 2,000 ከሚሆን የበጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ጋር ከፊታችን በሚከበሩ በመስቀል ዳመራና ኢሬቻ በዓላት ላይ ውይይትና የምክክር መድረክ አካሄደ።

****

መስከረም 10/2018 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ የከተማዋን ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ ህብረተሰቡን የሰላም ባለቤት ለማድረግና ዘላቂ ሰላምን በከተማዉ ለማስቀጠል ዘርፈ ብዙ ስራዎችን በመስራት ላይ ይገኛል።

ቢሮዉ በዛሬዉ እለት "በእምርታና ማንሰራራት የታጀበ ህዝባዊ በዓላትን በጋራ እናክብር" በሚል መሪ ቃል ከአዲስ አበባ ህብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን ጋር በመተባበር ለዚሁ ስራ የሚያግዙ ቁጥራቸው 2,000 ከሚሆን የበጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ጋር ከፊታችን በሚከበሩ በመስቀል ዳመራና ኢሬቻ በዓላት ላይ ውይይት የምክክር መድረክ አካሂዷል።

በዉይይቱ ላይም ክብርት ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ሀላፊ፣ክብርት ወ/ሮ ጸሃይ ኪባሞ የአዲስ አበባ ከተማ ህብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ምክትል ኮሚሽነር፣የተከበሩ አቶ ሚደክሳ ከበደ የሰላምና ጸ/ቢ/ም/ቢሮ ሀላፊን ጨምሮ የሚመለከታቸው የሁለቱም ተቋማት አመራሮች፣ሀደ ሲንቄዎች፣አባ ገዳዎች፣የሐይማኖት አባቶች፣ባለሙያዎች፣የሰላም ሰራዊት አባላት፣የአከባቢ ቅጥር ጥበቃ አባላት እና ከየ ክፍለ ከተማዉ የተወጣጡ በጎ ፈቃደኞች ተገኝተዋል።

በመድረኩ የመክፈቻ ንግግርና የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት ክብርት ወ/ሮ ጸሃይ ኪባሞ የአዲስ አበባ ከተማ ህብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ምክትል ኮሚሽነር ሲሆኑ፤በንግግራቸውም ከተማ አስተዳደራችን በእርግጥም የብልጽግና በር መሆኗን የሚያረጋግጡ ሰፋፊ ስራዎችን ሰርተናል በማለት ገልጸዉ፤ህብረተሰቡን መሠረት ያደረገ የሰላም እሴት ግንባታ ዘላቂነት ላይ ከአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ በጋራ እየሰራን የምንገኝ መሆኑ ዉጤቱም በሠራናቸዉ ስራዎች ይታያሉ ሲሉም ገልጸዋል።ም/ኮሚሽነሯ አያይዘውም ከፊታችን የሚከበሩትን የመስቀልና የኢሬቻ በዓላት ሰላማዊ ሆኖ እንዲከበር የበጎ ፈቃደኞችና የሰላም ሰራዊቱ፣የሀይማኖት አባቶች፣ሀደ ሲንቄዎችና አባገዳዎች፣የበጎ ፈቃደኞች እና አጠቃላይ ህብረተሰብ ከዚህ ቀደም ያሳዩትን የሰላም ግንባታ ሚናቸውን በዚህ አመትም እንዲደግሙ መልእክት አስተላልፈዋል።

የእለቱ የክብር እንግዳ ክብርት ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ በበኩላቸው፤ሀገራችን ኢትዮጽያ የባለብዙ ቅርስ ባለቤትና የራሷ ትዉፊቶችና ባህሎች ያሏት ሀገር እንደመሆኗ መጠን በቀጣይ በሚኒስኮ የተመዘገበውን የመስቀል እና በዩኒስኮ ለማስመዝገብ ሂደት ላይ ያለዉ የኢሬቻ በዓል ከአደባባይ በዓላት አንዱ ሲሆኑ በዓላቱም ትውፊታቸዉንና ዕሴታቸዉን ጠብቀው በሰላም እንዲከበሩ የሰላም ሰራዊትና የበጎ ፈቃደኞች ከፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት ህብረተሰቡን የሠላም ባለቤት በማድረግ በጋራ በመሆን በዓሉ በሰላም እንዲከበር ከዚህ ቀደም እንደሚደረገው በማድረግ መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል።

ከሰላም ሚኒስቴር የተገኙት ዶ/ር ገመቺስ ኢቲቻ በመስከረም ወር ላይ ኢትዮጵያዊነትን የሚገልጹ በተለያዩ አከባቢዎችና ክልሎች ላይ የሚከበሩ የመስቀል በዓልና ኢሬቻ ሃይማኖታዊና በህላዊ ቱውፊቱን የሚዳስስ ሰነድ በሰፊው አብራርተዉ አቅርበዋል።

የሰነዱን መቅረብ ተከትሎ ዉይይቱን የመሩት የተከበሩ አቶ ሚደክሳ ከበደና ክብርት ወ/ሮ ጸሃይ ኪባሞ ሲሆኑ፤ከተሳታፊዎች ሰፋ ያለ ሀሳብና አስተያየት አንስተዋል።

ዘመን ተሻጋሪ ድልን ከደሃ እናት መቀነት በመፍታት ከሊቅ እስከ ደቂቅ ተሳትፎ ይሄ ትዉልድ ዳግም አደዋን የጻፈበት አመት ላይ ሆነን አዲስ አመትን እያከበርን መሆኑ ያስደስታል ያሉት አቶ ሚደክሳ፤በዓላቱ ፍጹም ሰላማዊ ሆነዉ እንዲከበሩ ትልቅ ሀላፊነት ከናንተ ይጠበቃል ሲሉ ለበጎ ፈቃደኞቹ በአደራ መልክ አሳስበዋል።በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ተሳታፊዎች የሚሳተፉበት በዓል መሆኑ ጠላት እንዳይጠቀምበት የተለመደዉን የሠላም አምባሳደርነታችሁን እንድትወጡና ከተማችን ሰላሟ እንዲረጋገጥ በዓል እያከበርን ጎን ለጎን ሰላማችንን መጠበቅ አለብን ሲሉም አቶ ሚዴክሳ አመላክተዋል ።

በመጨረሻም ከሁለቱም ተቋማት ምክትል ቢሮ ሀላፊዎች ከበዓላቱ ጋር ተያይዞ በቀሪ ጊዜያት መከናወን ያለባቸዉን ዝርዝር ተግባራት በአቅጣጫ መልክ ተሠጥቶ መድረኩ ተጠናቋል።