የቀጠለ ዜና
የሰላም እሴትና መቻቻል ለሃገርና ትውልድ ግንባታ ያለው ፋይዳ በሚል መሪ ቃል በከተማ እና በክ/ከተማ ደረጃ ሲደረግ የነበረው ኮንፈረንስ የማጠቃለያ መርሐ ግብር ላይ ጥናታዊ ፅሁፍ ቀርቦ ውይይት ተካሄደ።
ህዳር 4/2018 ዓ.ም (ሰ.ፀ.አስ.ቢሮ)
****
በኮንፈረንሱ ላይ የሰላምና መቻቻል ዕሴቶችን ለትውልድ ግንባታ ስላላቸው ፋይዳ በተመለከተ መነሻ ጹሁፍና ጥናታዊ ምርምር ያቀረቡት ዶክተር ታምሩ ፈይሳ በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርስቲ መምህርና ተመራማሪ ሲሆኑ፣መነሻ ጹሁፉንና ምርምሩን ባቀረቡበት ወቅት የሰላም መቻቻል ባለበት ሀገር ውስጥ የሰላም ዕሴቶች ለትውልድ ግንባታ ያላቸው ፋይዳ እጅግ የጎላ እንደሆነና በትውልድ ቅብብሎሽ አንድ የሆነች ሀገር እንደሆነችም ጠቅሰው፣ስለሰላምና ግጭት ምንነት፣በሀገር ግንባታ፣ጥቅሞች እና ዕሴቶችን የሀገር ማንነት ጠብቆ የጋራ መሆናቸውን በመረዳት ለትውልዱ በማስተላለፍ የሃይማኖት አባቶች፣አባገዳዎች፣ሀደሲንቄዎች፣የሀገር ሽማግሌዎችና ታዋቂ ግለሰቦች ሚና የጎላ በመሆኑ የመቻቻል፣የአብሮነት እሳቤ በማስተላለፍ ሰላምን ማስቀጠል እንደሚገባ በሰነዱ አብራርተዋል።
መምህርና ተመራማሪው ዶ/ር ታምሩ ፈይሳ አክለውም እንደተናገሩት፣መንግስት የመቻቻልና የሰላም ዕሴቶችን አደጋ ላይ የሚከቱ ሁኔታዎች ከመከሰታቸው በፊት ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር መስራትና ለዚህም የሚተገበር ፖሊሲና መመሪያ ማዘጋጀት፣ፖለቲካዊና የገንዘብ ድጋፍ ማድረግ፣የሃይማኖት አባቶችና መሪዎች የሰላምና የመቻቻል ተምሳሌት መሆናቸውን ማረጋገጥ እና በሃይማኖት መካከል ትስስር መፍጠርና ማጠናከር የሚያስችል ስትራቴጂና መመሪያዎችን በማዘጋጀት ወደ ስራ መግባት፣አባገዳዎችና ሀደሲንቄዎችም በህዝብ ዘንድ ያላቸውን ተደማጭነት በመጠቀም ወጣቱ የአከባቢውን ሰላም እንዲጠበቅ መስራት፣የሰላምና የመቻቻል ዕሴቶችን ከሌሎች በተሻለ አጠናክሮ መቀጠልና የግጭት መንስኤዎችን በጋራ መፍታት እንዲሁም ወጣቶች ህዝቡን በማህበራዊ ትስስር የመቻቻል የመተባባር፣ከመንግስት አካላት ጋር መተማመን በመፍጠር አብሮ መስራት እንዳለባቸውም በሰነዱ አንስተዋል።
አቶ ፍሰሐ ጥበቡ የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ም/ል ቢሮ ሀላፊ በበኩላቸው የከተማችን ልማት ዕለት ከዕለት በተጨባጭ የሚታዩ የከተማዋን ክብሯን የሚመጥን ጉዞ እና ለውጥ ላይ እንደሆነች ጠቁመው፣ይህንን ልማት ለማስቀጠል የሃይማኖት ተቋማትና አባቶች፣አባገዳዎች እና ሁሉም የሚመለከተው አካል ምዕመናኑንና ወጣቱን እንዲሁም ልጆቻቸውን የመከታተል፣የማስተማር የመልካም ስነ-ምግባር ባለቤት የሆኑ ዜጎችን ማፍራት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።
ከከተማ የተሰጠውን ተልዕኮ በመውሰድ የሚተገብሩና የሚሰሩ ብዙ አመራሮች እንዳሉ ገልጸው፣አንዳንድ እኩይ ተግባራትንና ብልሹ አሰራር የሚሰሩ አመራሮችን ግልጸኝነትንና ተጠያቂነትን እየተገበርን ውስጣችንን በመፈተሽ ማስተካከያ እርምጃዎችን እንደሚወስዱም ተናግረው፣የምንጠቀማቸው ማህበራዊ ሚዲያዎችንም ለበጎ ስራዎች፣ለሀገር በቀል ዕሴቶቻችንን ለመገንባት፣ለሰላም ለአብሮነት መጠቀም እንዳለብን ሁሉም አካል የማስተማር ስራ ቢሰራና እንዲሁም ችግሮቻችንን በመወያየትና በመነጋገር የሀገራችንን ዕሴቶችና ባህሎችን አጠናክሮ በማስቀል ሁልጊዜ ለሰላም ቅድምያ በመስጠት እና የአባቶቻችንን ንግግር ሰውነት ይቀድማል የሚለውን በመከተል የሀገራችንን ህብረ ብሔራዊ በማስቀጠል ለመጪው ትውልድ የማትደፈር የምትከበር ሀገርን ማስረከብ ሁሉም የሚመለከታቸው አካላት ኃላፊነታቸውን መወጣት አለባቸው ሲሉ አቶ ብርሀኑ ረታ የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ጥሪ አቅርበዋል።