በወንጀል መከላከልና ሰነ-ምግባር ዙሪያ የአቅም ግንባታ ስልጠና ተሰጠ።
በወንጀል መከላከልና ሰነ-ምግባር ዙሪያ የአቅም ግንባታ ስልጠና ተሰጠ።
ህዳር 23/2018 ዓ.ም (አዲስ አበባ)
***
የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ የጸጥታ ኦፕሬሽን ዘርፍ ለጸጥታ አካላት እና ከማዕከል እስከ ወረዳ ለሚገኙ ለዘርፉ አመራሮችና ባለሙያዎች በወንጀል መከላከልና ሰነ-ምግባር ዙሪያ የአቅም ግንባታ ስልጠና ሰጥቷል።
መድረኩ ላይ በመገኘት የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ም/ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ወንድማገኝ ታደሰ፤ ሃገራችን ኢትዮጵያ በጸጋ የታደለች፣ ዳር ድምበሯን ጠብቃ ሳትደፈር የቆየች ታላቅና ድንቅ ሃገር ናትና ያላትን ፀጋና ሃብት በመጠቀም በልጽጋ ሌሎች ሃያላን ሀገራት የደረሱበት ለመድረስ ሰላም መሰረታዊ ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል።
ለሀገራችን ጦርነት ሳይሆን በሃሳብ በላይነት የሚያምን እና ሁሉም ነገር የሚከናወነው ሰላም ሲኖር ብቻ መሆኑን ተረድተው ለሰላም ቅድሚያ መስጠት ያስፈልጋል በማለት መንግሥታችንም ለዚህ ትኩረት በመስጠት እየሰራ መሆኑን ገልፀው፤ ወንጀል ሳይፈጸም ቀደም ብሎ በመከላከል ሁላችንም በመወያየትና በመነጋገር ለሰላም ቅድሚያ ሰጥተን የሰላም ዘብ መሆን እንደሚገባ ገልጸዋል።
ዶ/ር ወንድማገኝ አክለውም ወንጀልን ቀድሞ በመከላከል ነፍስ፣ ሀብትና በርካታ ነገሮችን ማትረፍ እንደሚቻልና የቅድመ መከላከል ስራችን ላይ ትኩረት በማድረግ መስራ ይገባናል በማለት አንስተዋል፡፡
ኮማንደር ገዛኸኝ ጌታነህ የአዲስ አበባ ፖሊስ የወንጀልና ትራፊክ አደጋ ጠቅላይ መምሪያ ምክትል ዳይሬክተር በበኩላቸው፤ የተለያዩ በዓላትና ሁነቶች ያለ ምንም የጸጥታ ችግር ተከብረው ማለፍ የተቻለው እና የተለያዩ ልማቶች ተሰርተው በዚህ ደረጃ መድረስ የተቻለው ጸረ ሰላም አካላት ችግር ለመፍጠርና ልማቱን ለማደናቀፍ ሳይፈልጉ ቀርተው ሳይሆን ፖሊስ እና ህዝብ ተቀናጅተው በመስራታቸው እና ትልቅ ጥበቃ በመደረጉ ነው ብለዋል።
ኮማንደር አክለውም አሁንም በርካታ ስራ የሚጠብቀን ሲሆን የከተማችን ነዋሪ ያለስጋት ወጥቶ እንዲገባ ለማድረግ ወንጀል መከላከልና ለወንጀል መንስኤዎችን ትኩረት መስጠት ይገባል ብለዋል።
ስልጠናውን የሰጡት ኢኒስፔክተር ካሊድ የማታው የአዲስ አበባ ፖሊስ የህዝብ ግንዛቤ ማስተባባሪያ ኃላፊ ሲሆኑ፤ የወንጀል ምንነት፣ የአፈንጋጭ ባህሪያት ትርጉም፣ ወንጀል ከአፈንጋጭ ባህሪያት ጋር ያለው አንድነትና ልዩነት፣ ወንጀል ነው ለማለት መሟላት ያለበት መስፈርት፣ ስነልቦናዊ የወንጀል መንስኤ እና የወንጀል መንስኤ በኢትዮጵያ ላይ ሰፊ ማብራሪያ ተሰጥተው ውይይት ተደርጎበታል።
በመድረኩ ላይም የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ም/ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ወንድማገኝ ታደሰ፣ የቢሮው ኃላፊ አማካሪ አቶ ዋቢ ጥላሁን፣ ኮማንደር ገዛኸኝ ጌታነህ የአዲስ አበባ ፖሊስ የወንጀልና ትራፊክ አደጋ ጠቅላይ መመሪያ ምክትል ዳይሬክተር፤ የአዲስ አበባ ፖሊስ ማህበረሰብ አቀፍ የጥናትና እቅድ ትንተና ዲቪዚዮን ኃላፊ ምክትል ኮማንደር ታዲዎስ አክሊሉ ፣ ኢኒስፔክተር ካሊድ የማታው የአዲስ አበባ ፖሊስ የህዝብ ግንዛቤ ማስተባባሪያ ሀላፊ፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ አመራሮችና አባላት እና ከማዕከል እስከ ወረዳ ለሚገኙ ለዘርፉ አመራሮችና ባለሙያዎች ተገኝተዋል።