የዉስጥ ለዉስጥ መንገዶች ላይ መብራት ማስበራት
ቢሮዉ ጨለማን ተገን በማድረግ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን ለመግታት በማለም በከተማዉ የዉስጥ ለዉስጥ መንገዶች ላይ መብራት የማስበራቱን ተግባር አጠናክሮ ቀጥሏል።
****
ታህሳስ 03/2018 ዓ.ም (ሰ.ፀ.አስ.ቢሮ)
የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ በከተማው አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍን ለማድረግ በእቅድ ላይ የተመሠረቱ በርካታ ስራዎችን 7/24 የሚል መርህን በመከተል እየሰራ መሆኑ አሙን ነዉ።
የእቅዱ አንድ አካል በማድረግም በአዲስ አበባ ከተማ ለቅሚያና ንጥቂያ መነሻ የሆኑና ለወንጀል የሚዳርጉ የዉስጥ ለዉስጥ መንገድ ጨለማ ስፍራዎችን ህብረተሰቡ ግንዛቤ እንዲወስድ በማድረግ አካባቢዎቹ ብርሃናማ እንዲሆኑ ለማድረግ ወደ ተግባር ከተገባ ሰነባብቷል ፤ቢሮዉ በተለያዩ ዙሮች ከማእከል አስከ ወረዳ ያሉ አመራሮችን ባሳተፈ መልኩ በተለያዩ ክፍለ ከተሞች በምሽት በመዘዋወር መብራት የማስበራት ስራ የሰራ ሲሆን፤ተጠናክሮ የቀጠለው ይኼዉ ተግባር በዛሬዉ እለት በቦሌ ክፍለ ከተማ አስተዳደር በመገኘት ከዚህ ቀደም በምሽት ለመንቀሳቀስ ስጋት የሆኑ አሁን ላይ ሙሉ በሙሉ ብርሃናማ የሆኑ ስፍራዎች ተዘዋውሮ የመስክ ምልከታ አድርጓል።
በአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ሀላፊ ከብርት ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ የተመራዉ የመብራት ማስበራት ግብረሃይል በክፍለ ከተማዉ ያሉ የተለያዩ ወረዳዎችን የብሎክ ዉስጥ መብራቶች ያሉበትን ሁኔታ የቃኘ ሲሆን፤
ክብርት ሀላፊዋ የመስክ ምልከታዉን ለማስጀመር ንግግር ባደረጉበት ወቅት እንደገለፁት፤የመብራት ማስበራት መርሃግብሩ ጨለማን በብርሃን የመተካትና በመስክ ምልከታዉ ወቅት አንዱ ክፍለ ከተማ ከሌላዉ ተሞክሮ በመቅሰም ከተማችን አዲስአበባ የአፍሪካ መዲና እንደ መሆኗ በርካታ የኢኮኖሚና ፓለቲካል እንቅስቃሴ የሚደረግባት ስለሆነ ወንጀልን በመቀነስ ዘላቂና አስተማማኝ ሰላምን ለማስፈን እንደሆነ አንስተዉ፤ከተማዋ የቱሪስት መዳረሻ እየሆነች መምጣቷ በቴክኖሎጂ የተደገፈ የከተማችን ሰላም፣ጸጥታና ደህንነት ለማረጋገጥ ህብረተሰቡን የሰላም ባለቤት በማድረግ ከጸጥታ መዋቅሩ ጋር በመቀናጀት ለወንጀል መንስኤ የሆኑ ቦታዎችን በመለየት የሚከሰቱ ወንጀሎችን የመቀነስ ስራ ተሰርቷል ሲሉም ገልጸዋል።
ሀላፊዋ አክለዉም ሰላም ወዳዱ ህብረተሰባችን የአከባቢዉን የበር ላይ መብራት ለማብራት ላደረገዉ አስተዋጽኦ በየደረጃው ያለ አመራር ደግሞ ተግባሩን በሀላፊነት ስላስተባበረ አመስግነዉ፤የብሎኪንግ ስራ የወንጀል ምጣኔን ከመቀነስ አኳያ ትልቅ አስተዋጽኦ ስላለው በ5446 የሚሆኑ አከባቢዎች ላይ ከአዲስ አበባ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ባለስልጣን ጋር በመቀናጀት እየተሰራ ስለሆነ በየ ብሎኩ በካሜራ የታገዘ ስራ በመስራት በቦሌ ክፍለ ከተማ የመጡ ዉጤቶችን የተሻለና የተጠናከረ የጸጥታ ስራ በከተማው መስራት እንደሚገባ አንስተዉ ህብረተሰቡም ከዚህ ቀደም ያሳየዉን የሰላም ባለቤትነት አጠናክሮ እንዲቀጥል ከአደራ ጭምር አሳስበዋል።
የቦሌ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶ/ር እሸቱ ለማ በበኩላቸው ያለፍት ጊዜያቶች ከተማችን ከልማት አኳያ ትልቅ ደረጃ ላይ ልትደርስ የቻለችዉ ሰላሟ ስለተጠበቀ ነዉ ያሉ ሲሆን፤የክፍለ ከተማው የጸጥታ አካላት ከህዝቡ ጋር ሆነዉ በርካታ ቀጠናዎች ከስጋት ነጻ መሆን እንዲችሉ ብዙ ስራ ተሰርቷል ብለዉ አንዳንድ ብሎኮች ካሜራ እንዲኖራቸው የማድረግ ስራ ብንሰራም በቀሪ ቦታዎች ላይ ደግሞ በቴክኖሎጂ የተደገፈ ስራ እንዲኖር በእቅድ ይዘን በመስራት ላይ እንገኛለንም ሲሊ ገልጸዋል።