የጥምቀት በዓል የጸጥታ ስራዎች አፈጻጸምን በመገምገም፤ 39ኛዉ የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ የፀጥታ ማስፈፀሚያ እቅድ ላይ ውይይት ተካሄደ።
የጥምቀት በዓል የጸጥታ ስራዎች አፈጻጸምን በመገምገም፤ 39ኛዉ የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ የፀጥታ ማስፈፀሚያ እቅድ ላይ ውይይት ተካሄደ።
****
ጥር 27/2018 ዓ.ም (ሰ.ፀ.አስ.ቢሮ)
የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮና የደንብ ማስከበር ባለስልጣን በጋራ በመሆን የ2018 ዓ.ም የከተራና የጥምቀት በዓል በሰላም መጠናቀቁን አስመልክቶ ከጸጥታ ግብረ-ኃይል ጋር የአፈፃፀም ግምገማ መድረክ አካሂዷል፤ በመድረኩም በበዓሉ የታዩ ጥንካሬዎችን በማስቀጠል በቀጣይ ለሚካሄደው የ39ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ እንደ ግብአት መውሰድ እንደሚገባ ተጠቁሟል።
የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ደንድር ባቀረቡት የጥምቀት በዓል አፈጻጸም ሪፖርት፤ በዓሉ ሃይማኖታዊ እሴቱንና ቅውፊቱን ጠብቆ እንዲከበር የማስፈጸሚያ ዕቅድ የጋራ ከማድረግ ጀምሮ በርካታ የዝግጅት ስራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል የፀጥታ አካላት፤ የሰላም ሰራዊት፣ የደብር አስተዳዳሪዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ወጣቶችና ሴቶች ከጸጥታ መዋቅሩ ጋር በቅንጅት በመስራታቸው ባጠቃላይ ህዝቡና ሌሎች አደረጃጀቶች የሰላሙ ባለቤት መሆን በመቻላቸዉ፤ በተለይም ከሸገር ከተማ አዋሳኝ አካባቢዎች ጋር የነበረው የተቀናጀ ስምሪት እና ከደንብ ማስከበር ኦፊሰሮች ጋር የተከናወነው ስራ ለበዓሉ ስኬት በዋናነት ተጠቃሽ እንደሆኑ አንስተዋል።
በመድረኩ የ39ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ የጸጥታ ማስፈጸሚያ ዕቅድ በአቶ ማስረሻ ሃብቴ የቀረበ ሲሆን፣ አዲስ አበባ የአህጉሪቱ ዲፕሎማሲያዊ ማዕከል እንደመሆኗ፣ ጉባኤው በሰላም እንዲጠናቀቅ የከተማዋን ነባራዊ ሁኔታ ያገናዘበና ሁሉንም የጸጥታ መዋቅር የሚያሳትፍ ስራ እንደሚሰራ ተመላክቷል።
የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ክብርት ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ ባስተላለፉት መልዕክት፤ በበዓሉ ወቅት የታየው የህዝብ ተሳትፎና የጸጥታ መዋቅሩ ቅንጅት የሚደነቅ መሆኑን በመግለጽ "ሪፖርቱን መገምገም ያስፈለገበት ዋና ምክንያት ጥንካሬዎችን ለመደበኛ ስራዎቻችን እንደ ግብዓት ለመጠቀምና የታዩ ክፍተቶችን ደግሞ በቀጣይ በሚኖሩ ትላልቅ አህጉራዊ ጉባኤዎች ላይ እንዳይደገሙ ለማድረግ ነው" ብለዋል።
ኃላፊዋ አክለዉም ክፍተቶችን ወደ ዜሮ በማውረድ ለታላላቅ ሁነቶች ዝግጁ መሆን እንደሚገባ አመላክተዉ መደበኛ ስራዎችን ዉጤት በሚያመጣ መልኩ መከወን ከቻልን ለትልልቁ ሁነቶች ትልቅ አቅም ይሆናል ያሉ ሲሆን ከህዝቡ የሠላም ባለቤትነት በተጨማሪ የሀይማኖት ተቋማት የሠላም ምንጭ በመሆናቸዉ በቅንጅት በመስራት የጸጥታና ደህንነት ስራ ማጠናከር እንደሚገባ አሳስበዋል።
የደንብ ማስከበር ባለስልጣን ስራ አስኪያጅ ሻለቃ ዘሪሁን ተፈራ በበኩላቸው፤ ባሳለፍነዉ የጥምቀት በዓል የድላችን ዉጤት የቅድመ ዝግጅት ስራችን የተሻለና ህዝቡን ከጎናችን ከማሰለፍ አንጻር የተሄደዉ ርቀት፣ የነበረዉ ከፍተኛ የህዝብ ንቅናቄ መድረኮች በዓሉ የፖለቲካ ፍላጎት ማንጸባረቂያ ሳይሆን ፍጹም ሰላማዊ በሆነ መንገድ ተከብሮ እንዲያልፍ አስችሏል ሲሉ ተደምጠዋል።
ስራ አስኪያጁ በንግግራቸዉ ደንብ ማስከበር ከጸጥታ መዋቅሩና ከህዝቡ ጋር ያለውን ቅንጅት ይበልጥ በማጠናከር የከተማዋን ጸጥታና ውበት ለመጠበቅ በቁርጠኝነት እንደሚሰራም ጨምረዉ ገልጸዋል።
በመድረኩ የሁለቱ ተቋማት ሀላፊዎችን ጨምሮ፣ የ11ዱም ክፍለ ከተማና የወረዳ ጽ/ቤት ሀላፊዎች የተገኙ ሲሆን፤ በመጨረሻም መድረኩን የመሩት ሁለቱ አመራሮች፤ ለ39ኛው የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ ስኬት ከማዕከል እስከ ወረዳ ያለው መዋቅር በሙሉ አቅሙ ወደ ተግባር እንዲገባ አቅጣጫ በመስጠት መድረኩ ተጠናቋል።