current news
የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ የመስቀል ደመራና የኢሬቻ በዓላት በሰላም እንዲከበሩ ለሰላም ሰራዊት ተወካዮች የግንዛቤ ማስጨበጫ፤ኦሬቴሽንና ስምሪት ተሰጠ።
መስከረም 12/2017ዓ.ም
(አዲስ አበባ)
********
የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ የ2017 ዓ.ም የመስቀል ደመራና የኢሬቻ በዓላት በሰላም ተከብሮ ያልፍ ዘንድ ለሰላም ሰራዊት አባላት ተወካዮች የግንዛቤ ማስጨበጫ፤ኦሬቴሽንና ስምሪት ሰጥቷል፡፡
በመድረኩ ላይ ተገኝተው የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ክብርት ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ ሲሆኑ በንግግራቸውም በከተማችን ውስጥ ሰላም ለማደፍረስ የሚንቀሳቀሱ ኃይሎችን ከፀጥታ አካላት ጋር በጋራ በመቀናጀት ትኩረት ተሰጥቶት መስራት ይገባል ብለዋል።
ክብርት ወ/ሮ ሊዲያ አክለውም ከፊታችን ሁለት ትላልቅ የአደባባይ በዓላት እንደሚከበሩ ጠቅሰው፣ወደ ከተማችን የሚገቡ በርካታ ቱሪስቶችና ዓለማቀፍ ሚዲያዎች በዓሉ ላይ ሲታደሙ ደህንነታቸው ተጠብቆ የበዓሉን ታላቅነት ለዓለም ህብረተሰብ እንዲያካፍሉ በነቃ ተሳትፎ አከባቢውን የመጠበቅ፣ የፀጉረ ልውጥ እንቅስቃሴ እንዳይኖር የማድረግ ስራ ለሰላም ሰራዊት አባል የተሰጠው ተልዕኮ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ለውይይት መነሻ የሆነውን ሰነድያቀረቡት የቢሮው የህብረተሰብ አደረጃጀት ዘርፍ ዳይሬክተር ወ/ሮ ፍሬሕይወት በለጠ ሲሆኑ፣ሰነዱን ባቀረቡበት ወቅት እንደተናገሩት የመድረኩ ዋና ዓላማ የ2017 ዓ.ም የመስቀል ደመራ እና የኢሬቻ ክብረ በዓላት የፀጥታ ስራዎች ከህብረተሰቡ፤ከፀጥታ ኃይሎች እና ከተለያዩ አደረጃጀቶች ጋር የተቀናጀና የተጠናከረ ተግባራት በማከናወን በዓላቱ ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲከበሩ ለማድረግ ነው ብለዋል፡፡
በውይይቱ ላይ የቢሮው ም/ል ኃላፊ አቶ ሚደክሳ ከበደ እንደተናገሩት ከተማችን ሰላም የሆነችው ጠላቶች ስለሌሉን አይደለም፡፡ታሪካዊ የባዳ ጠላትከውጪ፤እንዲሁም ከውስጥ ደግሞ ባንዳ የሆኑ ጠላቶች አሉብን፡፡ነገር ግን ህብረተሰቡ፤የፀጥታ ኃሎችና የሰላም ሰራዊቱ በጋራ ሆነን ከተማችንን በንቃት በመጠበቃችን ጠላቶቻችን አመቺ ሁኔታ ስላጡ እንጂ፤ስለዚህ አሁንም በርትተን ሰላማችንን ሌት ተቀን መጠበቅ አለብን ብለዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ክብርት ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ ውይየይቱን በመሩት ወቅት እንደተናገሩት ሁለቱም ኃይማኖታዊ የአደባባይ በዓላት ትውፊታቸውን ጠብቀው ተከብረው ለአገራችን ኢኮኖሚና ለአገር ገፅታ ግንባታ አስተዋፅዖ እንዲያደርጉ ቅድሚያ ሰላም መኖር አለበት ብለዋል፡፡
ከፊታችን የሚከበሩ ሁለቱ የአደባባይ በዓላት በሰላም እንዲከበሩ በየደረጃው የምትገኙ የሰላም ሰራዊት አባላት፣በየብሎካችሁ ከፀጥታ አካላት ጋር በመሆን መወያየት፣ለበዓሉ ስጋት ሊሆኑ የሚችሉ ጉዳዮች ካሉ ቶሎ ዕልባት መስጠት፣የተለያዩ የደንብ ጥሰቶች የሚፈፀባቸው ቦታዎችን፤እንደሺሻ ቁማር ቤቶች ወዘተ..መለየትና የማስተካከያ ዕርምጃመ ውሰድ፣ግጭት ቀስቃሽ ህትመት ዉጤቶችን ከሚያትሙ ድርጅቶች ጋር በቅድሚያ በመወያየት በዚህ ረገድ ያሉትን ሰጋቶች ማስወገድ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል፡፡
ክብርት ወ/ሮ ሊዲያ አክለውም የአደባባይ በዓላቱን ለማክበር በርካታ ህዝብ ወደ አደባባይ ከመውጣቱ ጋር ተያይዞ በከተማችን ብዙ ሃብት ፈሶበት የተሰራው የኮሪደር ልማት እንዳይበላሽ ከአዲስ አበባ ደንብ ማስከበር ባለስልጣን ኦፊሰሮች ጋር በመተባበር አስፈላጊውን ጥበቃ ማድረግ ይገባልም ብለዋል፡፡
በመድረኩ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ክብርት ወ/ሮ ሊዲያ ግርማን ጨምሮ የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ሚዴክሳ ከበደ፤ ዳይሬክተሮች፤ቡድን መሪዎችና ባለሙያዎች፤የክፍለ ከተማ ፅ/ቤት አስተባባሪዎችና ቁጥራቸው ከ660 በላይ የሆኑ የአዲስ አበባ ሰላም ሰራዊት ተወካዮች ተገኝተዋል፡፡