ኢትዮጵያ የብዝሃ-ሃይማኖት አገር ናት!!!
ኢትዮጵያ የብዝሃ-ሃይማኖት አገር ናት!!!
“የሃይማኖት ተቋማት በመደመር መንግሥት እይታ” በሚል መሪ ሀሳብ ዛሬም ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የሃይማኖት አባቶችና አመራሮች ጋር ፍሬያማ ውይይት አካሂደናል፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የዛሬዋን ኢትዮጵያ በመገንባት ረገድ ከሌሎች የሃይማኖት ተቋማት ጋር በመሆን ወሳኝ ሚና አበርክታለች። ቤተክርስቲያኗ በሀገረ መንግሥት ግንባታ፤ ጥንታዊ ቅርሶችን፣ ታሪኮችንና ትውፊቶችን ጠብቆ ለትውልድ በማሸጋገር፤ ትውልድን በማነጽ፤ ግብረ-ገብነትንና ሰብአዊ ርኅራኄን በማስተማር፤ የሕዝብ ለሕዝብ ትስስርን በማጠናከር እንዲሁም በልማት ተሳትፎ የጎላ ድርሻ ስትወጣ ቆይታለች።
በታሪክ ብቻ ሳይሆን ባለፉት የለውጥ ዓመታትም ቤተክርስቲያኗ በከተማችን ሁለንተናዊ የሰላም ግንባታ፣ የልማት እና የብልፅግና ጉዞ ላይ እያበረከተች ያለውን አስተዋጽኦ አንስተን የተወያየን ሲሆን፣ ለሕዝቦች ትስስር መጎልበት፣ ለሰላም ፣ ለኢትዮዽያ ብልፅግና እና ለብሔራዊ ጥቅም በጋራ ለመቆም መግባባት ላይ ደርሰናል።
የዉይይት መድረኩ፣ የተነሱ አንዳንድ ያጋጠሙ ክፍተቶችን በትብብር ለማረም የሚያስችል ምቹ መደላድል የፈጠረ ውጤታማ መድረክ ነበር። ይህ መድረክ በየክፍለ ከተማው ሲካሄዱ የቆዩ ውይይቶች ማጠቃለያ ሲሆን፣ የመንግሥትንና የሃይማኖት ተቋማትን ሚና እና ድርሻ በግልጽ ለይቶ ያስቀመጠ ነው።
ክቡራን የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አባቶችና አመራሮች፤ ላደረጋችሁት ከፍተኛ ተሳትፎና ለሰጣችሁን ገንቢ ሐሳብ በራሴና በከተማ አስተዳደሩ ስም ከልብ አመሰግናለሁ።
መልካም የአብይ ጾም!
ፈጣሪ ኢትዮጵያን እና ሕዝቦቿን ይባርክ!