የሰላም ሰራዊት ምርቃት
ቢሮው ለ10 ቀናት በንድፈ ሃሳብና በወታደራዊ መስክ ያሰለጠናቸውን 11,000 አዲስ ምልምል የሰላም ሰራዊት አባላትን አስመረቀ፡፡
መስከረም 22/ 2017 ዓ.ም
(አዲስ አበባ)
****
የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ለ10 ቀናት በንድፈ ሃሳብና በወታደራዊ መስክ ያሰለጠናቸውን አሥራ አንድ ሺ አዲስ ምልምል የሰላም ሰራዊት አባላትን በአበበ ቢቂላ ስታዲየም አስመረቀ፡፡
በመርሃ-ግብሩ መጀመሪያ ላይ ንግግር ያደረጉት የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ክብርት ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ እንደተናገሩት ለከተማችን ደረጃዋን የሚመጥን ሰላም ፀጥታና የህግ በላይነት ሊያስከብሩ የሚችሉ ዘመናዊ የፀጥታና ህግ አስከባሪ ተቋማት ሊኖሯት ይገባል ብለዋል።ክብርት የቢሮ ኃላፊዋ አክለውም ቢሮው ተግባርና ሃላፊነቱን ከሌሎች ህግ አአስክባሪ ተቋማት ጋር በመቀናጀትና ማህበረሰቡን በማሳተፍ የከተማውን ሰላም በመጠበቁ የአደባባይ በዓላት በሰላም ተከብረው እንዲያልፉ ለማድረግ ተችሏል ብለዋል፡፡
በከተማዋ የሰላም ሰራዊት አባላት ሥራ ከጀመሩ ጊዜ ወዲህ የወንጀል ክስተት ምጣኔ የመቀነሱንም ክብርት ወ/ሮ ሊዲያ ተናግረዋል፡፡
በምረቃ መርሃ-ግብሩ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው ባደረጉት ንግግር ከተማዋ የአስተማማኝ ሰላም ባለቤት የሆነችው በሰላም ሰራዊቱ ፣ በፀጥታ ተቋማትና በነዋሪዎች ቅንጅት በመሆኑ ሊመሰገኑ ይገባልም ብለዋል።
የሰላም ሰራዊት አደረጃጀት የኢትዮጵያ አንድነት ማሳያ መሆኑን እና ቀንና ሌሊት ሳይሰለቹ በንቃት አከባቢያቸውን በመጠበቅ የከተማውን ሰላም የሚያረጋግጡ መሆናቸውን የገለፁት ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ የህዝብ አደረጃጀት ዘርፍ አቶ ሚደክሳ ከበደ ናቸው።
በመጨረሻም ስልጠና በመስጠትና የተለያዩ ድጋፎችን ሲያደርጉ ለነበሩ ተቋማት ላበረከቱት አስተዋጽኦ ዕውቅና የተሰጣቸው ሲሆን ተመራቂዎቹ ከሌሎች የፀጥታ ተቋማት ጋር በመሆን የከተዋን ሰላም ዘላቂ ለማድረግ በፍፁም ትጋት፤ታማኝነትና ቅንነት ሃላፊነታቸውን ለመወጣት ቃል ገብተዋል።
በምረቃ መርሃ-ግብሩ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ክብርት ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ፤
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ስተዳደር ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ወንድሙ ሴታ፤
የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ም/ቢሮ ኃላፊዎች፣ የአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው፤የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮች፤የክፍለ ከተማና የወረዳ ሰለምና ፀጥታ አስተዳደር ፅ/ቤት ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡