በህብረ-ብሔራዊነት ላይ ያተኮረ የአሰልጣኞ ስልጠና ተሰጠ።
ብዝሃነት ለሀገር ግንባታ፣ ትምህርት ለዘላቂ ሰላም እንዲሆን በማለም ለከተማዉ የስነ-ዜጋና ስነ-ምግባር መምህራንና ለሰላም እሴት ግንባታ ዘርፍ አስተባባሪዎች በህብረ-ብሔራዊነት ላይ ያተኮረ የአሰልጣኞ ስልጠና ተሰጠ።
***
መጋቢት 26/2018 ዓ.ም (አ.አ.ሰ.ፀ.አስ.ቢሮ)
የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ የሃይማኖትና ሰላም እሴት ግንባታ ዘርፍ ከአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮ ጋር በመቀናጀት፤ ከማእከል እስከ ወረዳ ላሉ የዘርፉ አስተባባሪዎችና በሁሉም ክፍለ ከተማ ለሚገኙ ለስነ-ዜጋና ስነ ምግባር መምህራን ብዝሃ ባህላዊነት ለሀገረ መንግስት ግንባታ ያለዉ ሚና እና ግብረገብነት ላይ ያተኮረ ስልጠና ተሰጠ።
የመድረኩ ዋና ዓላማ መምህራን በብዝሃ-ባህላዊነትና በህብረ-ብሔራዊ ንድፈ-ሀሳብ መሠረቶች ላይ ያላቸውን ግንዛቤ በማሳደግ፣ ይህንኑ እውቀት ወደ ተማሪዎች ለማሸጋገር ቀጣይ ከየ ክፍለ ከተማዉ ትምህርት ጽ/ቤቶች ጋር በመቀናጀት የወሰዱትን የአሰልጣኞች ስልጠና/TOT/ በትምህር ቤቶች ዉስጥ የሚገኙ መምህራን ጭምር በማሠልጠን የነገዋን ሰላማዊት ኢትዮጵያ በፅኑ መሠረት ላይ ለመገንባት ስለመሆኑ በመድረኩ ሲነሱ የነበሩ ርዕሰ ጉዳዮች አመላካች ናቸዉ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊና የዘርፉ አስተባባሪ አቶ ተስፋዬ አበራ በከተማ አስተዳደሩ አዲሱን ስርአተ ትምህርት መሰረት በማድረግ ተግባራዊ ከተደረጉ ትምህርቶች መካከል አንዱ የግብረገብ ትምህርት መሆኑን አስታውሰው ትምህርቱ በስነምግባር የታነጸና የሀገሩን እሴቶች የሚያከብር ትውልድ መፍጠርን መሰረት አድርጎ ተግባራዊ እንደመሆኑ ትምህርቱን የሚያስተምሩ መምህራን በሀገረ መንግስት ግንባታ እና በብዝሐነት ጽንሰ ሀሳብ ዙሪያ ለተማሪዎች በቂ ግንዛቤ በመፍጠር ሀገሩን የሚወድ ትውልድ ለማፍራት የሚከናወነው ተግባር ውጤታማ እንዲሆን የበኩላቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
ስልጠናዉን የሰጡት የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ የሐይማኖትና ሰላም እሴት ግንባታ ዘርፍ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሙሉቀን እንየዉ ሲሆኑ፤ሀገረ መንግስትና ሀገረ ብሔር ላይ ያተኮረ የስልጠና ሰነድ አቅርበዉ ብዝሃነት የውበታችን ብቻ ሳይሆን የጥንካሬያችን ምንጭ ነው በማለት ህብረ-ብሔራዊነትን እንደ ንድፈ-ሀሳብ ብቻ ሳይሆን እንደ ዕለት ተዕለት መመሪያችን ልንወስደው ይገባልም ብለዋል። በተለይ በጋራ ማንነት ላይ ያተኮረ ፅንሰ-ሀሳብን በትምህርት ቤቶች ውስጥ ማስረፅ ከተቻለ፣ ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ አጋዥ የሆነና ሌላውን የሚያከብር ትውልድ መፍጠር እንደሚቻል አሳስበው፤መምህራን የዚህ ታላቅ ሀገራዊ ተልዕኮ ግንባር ቀደም መሃንዲሶች እንዲሆኑም አመላክተዋል።
ዳይሬክተሩ አክለዉም በሀገረ መንግስት ግንባታ ሂደት በትምህርት ገበታ ላይ ብዝሃ-ባህላዊነትን በማስተማር ተማሪዎች የራሳቸውን ማንነት እያከበሩ የሌላውን ልዩነት እንደ ጸጋ እንዲቀበሉ ማስቻል ስለመሆኑ ገልጸዉ፣ የስልጠናው ዓላማ የህብረ-ብሔራዊነት ይዘት በማስገንዘብ ፣ ተማሪዎች ከአግላይነት ወጥተው ለአካታችነት ቅድሚያ እንዲሰጡ የሚያደርግና መምህራን በትምህርት ቤቶች ውስጥ የዴሞክራሲ እሴቶች እንዲጎለብቱና ተማሪዎች በጋራ እሴቶች ላይ ተመስርተው እንዲያድጉ የማድረግ ከፍተኛ ኃላፊነት እንዳለባቸው አንስተዋል።
የ11ዱም ክፍለ ከተማ የሰላም እሴት ግንባታ ዘርፍ አስተባባሪዎች የተሳተፉበት ይሀዉ ስልጠና ላይ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ከትምህርት ቢሮ የተገኙ አሰልጣኞች በሰነድ መልክ ያቀረቡ ሲሆን የስልጠናው ዋና ዋና ይዘቶችም፣ግብረ ገብነት፣የህብረ-ብሔራዊነት ንድፈ-ሀሳብ በብዝሃነት ውስጥ ያለን አንድነት እንዴት ሀገራዊ ሉዓላዊነትን እንደሚያጠናክር፣የጋራ ማንነት ግንባታ በልዩነቶች መሃል ያሉን የጋራ እሴቶች ቋንቋ፣ ታሪክ፣ ማህበራዊ ትስስር ለሰላም ግንባታ በመጠቀም ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ያለው ሚና በስፋት ተዳሶ ህብረ-ብሔራዊነትን ማክበር ለፍትሃዊነትና ለዴሞክራሲ መስፈን ያለውን አይተኬ ሚና ላይ ግንዛቤ ተፈጥሯል።
በማጠቃለያው ላይ፣ ሰልጣኝ መምህራንና አስተባባሪዎቹ
ባገኙትን ግንዛቤ በተግባር በመተርጎም በቀጣይ በትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚገኙ መምህራንና የሰላምና የብዝሃነት ክለቦች አባላትን ታች ድረስ በማሠልጠን መምህራን በክፍል ውስጥና በክፍል ውጭ በሚያደርጉት እንቅስቃሴ የተማሪዎችን የሰላም ግንባታ አቅም በማሳደግ ለተማሪዎች አርአያ ለመሆን መግባባት ላይ በመድረስ መድረኩ ተጠናቋል።
#አዲስ_አበባ #ሰላምና_ፀጥታ #ትምህርት_ቢሮ #ብዝሃነት #ህብረ_ብሔራዊነት #የሰላም_እሴት
https://linktr.ee/qr/e5702bda-a953-4926-8253-c3bd2f978c79