የሀገራዊ ምክክር ሂደቱ በሠላም እንዲጠናቀቅ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት አጠናቆ ወደ ስራ መግባቱን ጥምር የፀጥታና ደህንነት ኃይል አስታወቀ፡፡
የሀገራዊ ምክክር ሂደቱ በሠላም እንዲጠናቀቅ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት አጠናቆ ወደ ስራ መግባቱን ጥምር የፀጥታና ደህንነት ኃይል አስታወቀ፡፡
ሐምሌ 01 ቀን 2018 ዓ/ም
በአዲስ አበባ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ሌ/ጀነራል አስራት ደኔሮ፣ በሠላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ክብርት ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ እና በፌደራል ፖሊስ የፀጥታና ተቋማት ጥበቃ ዋና መምሪያ አዛዥ ም/ኮሚሽነር አበራ ሁንዴ በተመራው የጥምር ኃይሉ የፀጥታ ጥበቃ ዕቅድ ውይይት ላይ የአዲስ አበባ ከተማ ደንብ ማስከበር ባለ ስልጣን ዋና ስራ አስኪያጅ ሻለቃ ዘሪሁን ተፈራ፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ም/ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ም/ኮሚሽነር ቶፊቅ መደድ፣ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት፣ የክ/ከተማ ፖሊስ መምሪያና ዋና መምሪያ አዛዦች እንዲሁም ሌሎች የፀጥታ አካሉ አመራሮች ተገኝተዋል፡፡
ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ/ም ጀምሮ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በከተማችን አዲስ አበባ በሚካሄደው ሀገራዊ ምክክር ለመሳተፍ ከተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች የሚመጡ ተሳታፊዎች ጉባኤውን በሠላም እንዲያከናውኑ ተገቢው የፀጥታ ጥበቃ ስራ እንደሚደረግ የገለፁት የአዲስ አበባ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ሌ/ጀነራል አስራት ደኔሮ ይህ የውይይት መድረክ ሀገሪቱን ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሻግር በመሆኑ ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶት እንደሚሰራ ገልፀዋል፡፡
በየደረጃው የሚገኘው የፀጥታ ኃይል በላቀ ቁርጠኝነት ጉባኤው እንዲሳካም የበኩሉን አስተዋፅኦ ሊወጣ እንደሚገባም ሌ/ጀነራል አስራት አሳስበዋል፡፡
ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ የአዲስ አበባ ከተማ ሠላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ እንደገለፁት በ ጉባኤው ልዩ ልዩ የፖለቲካ አመለካከቶችን የሚያራምዱ በርካታ ተሳታፊዎችን ያቀፈ እንደመሆኑ መጠንና ከጉባኤው መካሄድ አስቀድሞ ተሳታፊዎች በከተማዋ የተከናወኑ የልማት ስራዎች ላይ በሚያደርጓቸው ጉብኝቶች ከሠላም ሰራዊትና ከልዩ ልዩ አደረጃጀቶች ጋር በመሆን ጠንካራ ስራ እንደሚሰራ አብራርተው ጉባኤው ላይ ለሚሳተፉ ግለሰቦች የጋራ ደህንነት ሲባል ፍተሻ እንደሚኖር ተናግረዋል።
ከምክክር ሂደቱ ጎን ለጎን ሀገር አቀፍ ፈተና የሚከናወንበት ወቅት እንደመሆኑ መጠን ስራው ትኩረት ተሰጥቶበት ይሰራል ያሉት ደግሞ የፌደራል ፖሊስ የፀጥታና ተቋማት ጥበቃ ዋና መምሪያ ኃላፊ ም/ኮሚሽነር አበራ ሁንዴ፤ ተሳታፊዎች ይዘዋቸው በሚመጡት ልዩ ልዩ ባንዲራዎችና መለያዎች ላይ ክልከላ እንደማይደረግ ተናግረው ይህ ጉባኤ ልዩነቶቻችን በውይይት የሚፈታበትና ለነገዋ ኢትዮጵያ ታላቅ የምስራች ይዞ የሚመጣ በመሆኑ በልዩ ትኩረት ይሰራል ብለዋል፡፡
የቀረበው የጥምር የፀጥታ ኃይሉ ዕቅድ ላይ ተገቢው ውይይት የተደረገ ሲሆን ተሳታፊ አመራሮችም ዕቅዱን ወደ ተግባር በመቀየር ይህ ታሪካዊ ጉባኤ ፍፁም ሠላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡
ለተነሱ ማብራሪያ የሚሹ ሀሳቦችም ከመድረክ ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡
*
ዘገባው የአዲስ አበባ ፖሊስ ነው ፡- በረ/ኢንስፔክተር ዳዊት እርገጤ