ወጣት ማህበር አባላት

image description
- recent news   

ወጣት ማህበር አባላት

አዲስ አበባችን ዘላቂ ሰላም የሰፈነባት፤ንጹሕና ለኑሮ ምቹ የማድረግ ስራው በቀጣይም ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል ።

 አቶ ሚደቅሳ ከበደ የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ም/ቢሮ ሀላፊ 

           ጥቅምት 25/2017 ዓ.ም 

                 አዲስ አበባ

                  ******
ም/ቢሮ ኃላፊው ይህንን የተናሩት  የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ የህዝብ አደረጃጀት ዘርፍ ከአስራ አንዱም ክ/ከተማ ለተወጣጡ ወጣት ማህበር አባላት ግጭትን መከላከል፤ ማስተዳደርና ሰላምን በመገንባት ዙሪያ  የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና በሰጠበት መድረክ ላይ ነው ።

አቶ ሚደክሳ ከበደ በግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኩ ላይ ለተገኙት ወጣቶች የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉ በዚህን ወቅት  እንደተናገሩት፦አሁን ላይ በተለያየ ግዜ በአዲስ አበባ ከተማ  ላይ ስለ ሰላም በመወያየት ዘላቂ ሰላምን ማምጣት ተችሏል ነው ያሉት፤ ም/ቢሮ ኃላፊው አክለውም አዲስ አበባ ከተማ  ያስተናገደቻቸው ትላልቅ የአደባባይ ብሔራዊ እና ህዝባዊ በዓላቶች ያለ አንዳች የጸጥታ ችግር ማለፋቸው  ምስክር እንደሆነ ሁሉ አሁንም ከተማውን በሚመጥን መልኩ በወንድማማችነትና አብሮ በመሆን በዓላት በሰላም ተከብረው  የከተማዋ የቱሪስት እንቅስቃሴ ጨምሮ የገቢ ምንጭ እንዲሆን የማድረግ ስራ መሰራቱንም ጭምር  በመግለፅ ጠላቶቻችን ህዝብን ለማጋጨት ብዙ ቢሰሩም አጠቃላይ ማህበረሰቡን የሰላም ባለቤት በማድረግ የከተማዋ ሰላም ዘላቂና አስተማማኝ የማድረጉ ስራ  ተጠናክሮ መቀጠል ይገባዋል ፤ ወጣቱ ትውልድ የከተማው የጸጥታ አጋዥና መረጃ  ምንጭ በመሆን የሰላምና ጸጥታው ስራ ዘላቂ እንዲሆን የወንጀል ምጣኔን ከመቀነስ አንፃር የወጣቱ ሚና አሁን ካለው ሁኔታ የላቀ ሊሆን ይገባል ብለዋል፡፡

ለውይይቱ መነሻ የሆነውን ሰነድ ያቀረቡት የዘርፉ የስልጠና ባለሙያ አቶ ውድነህ አቢ እንዳሉት ሰላም የሚጀምረው ከራስ እንደመሆኑ ሁሉ ግጭት ተፈጥሯዊ መሆኑን በመረዳት ልናስወግደው እንኳን ባንችል ልንከላከልና ልንቀንሰው እንችላለን ፡፡ በመነጋገርና በመከባበር መንፈስ የግጭት መንስኤዎችንና ችግሮችን  መፍታት ይገባል ብለዋል፡፡ 

ባለመግባባት ውስጥ በሚፈጠር የግጭት መንስኤ የሰው ልጅ ህይወት መጥፋት አላስፈላጊም ነው፤ ኢትዮጵያ ግጭትን ለመከላከልና ለመቀነስ የሚያስችሉ የተለያዩ  ባህልና ወግ ያላት ሲሆን አንዱ አንዱን ደግፎ የሚታይበት እንደ መሆኑ ያለመግባባቶችን ወደ ጎን በመተው የሀሳብ ልዩነቶችን ወደ አንድ በማምጣት ባህላዊዉንና ሳይንሳዊ መንገዶችን በመጠቀም መከለከልና ማስተዳደር ይገባል በማለት ሰነዱን መነሻ በማድረግ አብራርተዋል።

ከሰነዱ ማብራሪያ በኃላ መድረኩን የመሩት አቶ ታዬ ሽፈራው የቂርቆስ ክ/ከተማ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ፅ/ቤት ሃላፊ እንደተናገሩት ከተማዋን ሰላም ለማድረግ ስናስብ ወጣቱ የራሱን ተሳትፎ በማድረግ ከጸጥታው ሀይል ጋር በመሆን ለሀገራችን የሰላም ዘብ ሊሆን ይገባል ብለዋል ።

አቶ ገዛኸኝ ገ/ማርያም  የአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶች ማህበር ፕሬዝዳንት በበኩላቸው ሰላማችንን በማጠናከር እየተሰሩ  ያሉት እንቅስቃሴዎች ላይ  በመሳተፍ የሚነሱ ጥያቄዎች ለመመለስ በየቦታው በሚገኙ የሰላም ክበባት ላይ ተሳትፎ በማድረግ  በከተማው ላይ የተጀመሩ የልማት እንቅስቃሴዎች ውጤታማ እንዲሆኑ የከተማው ወጣት ተሳትፎ  ስለሚያስፈልግ በሰላም ዙሪያ አብሮ መስራት ተገቢ መሆኑን ጠቁመዋል።