በሴኩላሪዝም ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ
ቢሮው በሴኩላሪዝም ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ሰጠ።
ጥቅምት 26/02/2017 ዓ.ም
አዲስ አበባ
የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ የሃይማኖት ተቋማት ጉዳዮችና የሰላም ዕሴት ግንባታ ዘርፍ በህገ-መንግስቱ የሴኩላሪዝም ፅንሰ ሃሳብ ዙሪያ ከሁሉም ክፍለ ከተማዎችና ወረዳዎች ለተውጣጡ የትምህርት ቤቶች ሱፐርቫይዘሮችና ባለሙያዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ሰጥቷል፡፡
የስልጠናውን ሰነድ ያቀረቡት የሰላም ዕሴት ግንባታና የሃይማኖት ጉዳዮች ዘርፍ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ተመስገን እጅጉ ሲሆኑ፣በገለፃቸውም የሴኩላሪዝም ምንነት፣የኢፌድሪ ሴኩላሪዝም ድንጋጌዎች፣በሴኩላሪዝም አተገባበር የሚታዩተግዳሮቶች፣ጉድለቶች፣
የእምነት እኩልነት፣ሰላምና ልማትን ማስከበርና ማክበር የህገ መንግስቱ መሰረታዊ መርሆች እንደሆኑ አብራርተዋል።
መንግስት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ እንደማይገባ ሃይማኖትም በመንግስት ጉዳይ ጣልቃ እንደማይገባ በህገ-መንግስቱ የተደነገገ እንደሆነ አቶ ተመስገን በማብራሪያቸው ገልጸዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ም/ቢሮ ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ጫኔ ዉይይቱን በመሩበት ወቅት እንደተናገሩት የዛሬው መድረክ በዋናነት በመማር ማስተማር ሂደት ውስጥ በበላይነት የምታስተዳድሩ እንደመሆናችሁ መጠን ትልቅ ድርሻ ስላላችሁ በዚህ አከባቢ ያለውን ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደትን ለማስቀጠል ያለመ ነው ብለዋል።
በቀጣይም ከት/ቤቶች ሱፐርቫይዘሮች፣ከክ/ከተሞችና ወረዳዎች ባለሙያዎች ጋር ዕቅዳችንና ስራችንን ማዕከል በማድረግ በጋራ እየተወያየን የምንሠራ ይሆናል ሲሉ አቶ ተስፋዬ ገልጸዋል።
በት/ቤቶች ውስጥ የሚገኙ ሁሉም አካሎች በግቢ ውስጥ ተማሪዎች የሚያደርጉትን እንቅስቃሴዎችና አዝማሚያዎች መከታተልና የሚነሱ ጥያቄዎች ትኩረት ሰጥቶ በወቅቱ ምላሽ መስጠት ይገባል ሲሉ ም/ል ቢሮ ኃላፊው አሳስበዋል።
በመድረኩ ላይ የቢሮው ም/ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ጫኔን ጨምሮ የሰላም ዕሴት ግንባታና የሃይማኖት ጉዳዮች ዘርፍ ዳይሬክተር ቡድን መሪዎችና የክፍለ ከተማ አስተባባሪዎችም ተገኝተዋል፡፡