ለቢሮው የማዕከል ሰራተኞች ስልጠና ተሰጠ።
በጫኝና አውራጅ ማህበራት አገልግሎትአሰጣጥ ዙሪያ ለቢሮው የማዕከል ሰራተኞች ስልጠና ተሰጠ።
ህዳር 10/ 2017 ዓ.ም (አዲስ አበባ)
*****
የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ የህዝብ አደረጃጀት ዘርፍ በጫኝና አውራጅ ማህበራት አገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ ለቢሮው የማዕከል ሰራተኞች ስልጠና ሰጥቷል።
የሥልጠናው ዋና ዓላማ የቢሮው ሰራተኞች አገልግሎቱን በሚሰጡ ማህበራት አማካይነት የሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በማወቅ የህግ ማስከበር ሥራዎች ሲሰሩ የቢሮው ሰራተኞች የድርሻቸውን እንዲወጡ ለማድረግ እንደሆነ በስልጠናው ወቅት ተጠቅሷል፡፡
መድረኩ ላይ መመሪያውን መሰረት አድርጎ የተዘጋጀውን ማብራሪያ ያቀረቡት የዘርፉ ዳይሬክቶሬት ባልደረባዎች የጫኚና አውራጅ ተግባርና ሃላፊነት እና የባለድርሻ አካላት ሚና ፣ የቢሮው ሚና፣ስለእርምጃ አወሳሰድና አቤቱታ አቀራረብ፣ ለመደራጀት የተደረገው ጥናት፣ የጥናቱ አለማ እና ግብ የዋጋ ተመን ዝርዝር ...ወዘተ አብራርተዋል።
በስልጠናው ወቅት ለቀረቡት ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት የዘርፉ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ተወካይ አቶ አብረሃም እንግዳወርቅ እንደተናገሩት ካሁን በፊት በአገልግሎት አሰጣጡ ዙሪያ በርካታ የህዝብ ቅሬታዎችና አቤቱታዎች የሚቀርቡበትና ለግጭትና ለፀጥታ ስጋት የነበረ ሲሆን መመሪያውን መተግበር ከተጀመረ ወዲህ ግን ዘርፉ ከስጋት ወደ ፀጥታ ኣጋርነትና ወደ ልማት መቀየር መቻሉ ትልቅ እምርታ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ተወካዩ አክለውም በመመሪያው ላይ አጠቃላይ የቤት ዕቃዎች የዋጋ ተመን የወጣ ሲሆን የዋጋ ተመኑ እንደወቅቱ የኑሮ ሁኔታ አስፈላጊ በሆነ ጊዜ መሻሻል የሚችል ሲሆን የቢሮው ሰራተኞች መመሪያውን በማስከበር ረገድ የድርሻቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።