የስምምነት ሰነድ መፈራረምያ መረሃ-ግቢረ
ከሸገር ሲቲ ጋር በቅንጅት በመስራታችን ድንበር ተሻጋሪ የሆኑ ወንጀሎችን ለመቀነስ ተችሏል።
ክብርት ወ /ሮ ሊዲያ ግርማ የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ሀላፊ ።
ታህሳስ 10/ 2017 (አዲስ አበባ )
******
ክብርት የቢሮ ኃላፊዋ ይህንን የተናገሩት የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ እና የሸገር ከተማ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ጽ/ቤት በሰላምና ጸጥታ ጉዳዮች ዙሪያ በጋራ የሰሩትን ስራ በገመገሙበትና በቀጣይም አብረው ለመስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ሰነድ በተፈራረሙት ወቅት ነው።
ክብርት ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ እንዳሉት በሁለቱም ከተሞች ላይ አስተማማኝ ሰላምና ጸጥታ ደህንነቷም የተረጋገጠባት ከተማ ለማድረግና ጸጥታው ቀጣይነት እንዲኖረው በተሰራው ሥራ የመጣው ለውጥም እንዲፀና ከአጎራባች ከተሞች ጋር በቅንጅት በመስራት ድንበር ተሻጋሪ የሆኑ ወንጀሎችን ለመቀነስም መቻሉን ተናግረዋል፡፡
አክለውም ከአጎራባች ከተማዎች የጸጥታው ሀላፊዎችም ጋር በመቀናጀት በርካታ የአደባባይ በዓላት በሰላም ለማክበር ከመቻሉም ባሻገር በንግዱ ዙሪያ የኢኮኖሚ አሻጥር እንዳይፈጠር ብሎም ህገ-ወጥ እንቅስቃሴዎችን መቀነስ መቻሉንም ገልፀዋል፡፡
በመጨረሻም ከጸጥታው ጎን ለጎን በኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች፣የጽንፈኛ ሀይሎችን ሴራ የማክሸፍ ተግባራት ላይ ከምን ግዜውም በበለጠ መልኩ በጋራ በመስራት አዲስ አበባ ከተማ የሰላም ተምሳሌትነቷን አጉልቶ በማጽናት ውስጥ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል በማለት ክብርት የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ሀላፊዋ ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ አጽንኦት ሰተው ተናግረዋል።
በሁለቱ ከተሞች መካከል በጋራ የተሰሩትና ለውጥ የመጣባቸውን ጉዳዮች በተመለከተ ሰነድ ያቀረቡት ኮማንደር ሙሉጌታ በጋሻው የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ የጸጥታና ኦፕሬሽን ዘርፍ ዳይሬክተር ናቸው፡፡
አቶ ጉዮ ገልገሎ በኦ/ብ/ክ/መ/የሸገር ከተማ አ/ም/ከንቲባና የኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪ በበኩላቸው፦ ሰላም የሁሉም መሰረት እንደመሆኑ መጠን በበለጠ መልኩ ደግሞ ዘላቂ ሰላምን ለማግኘት ዋጋ እንደሚያስከፍል በማወቅ የጸጥታ መዋቅር ብቻ ሳይሆን ሁሉም በተሰማራበት ቦታ ሀላፊነትን በመውሰድ ከከተማ አስተዳደሮች ጋር በመሆን የተጀመሩ የልማት ስራዎች ቀጣይነት እንዲኖራቸው ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመው የሰላም ጥሪውን በመቀበል ወደ ተፈለገው የሰላም መንገድ የገቡ አካላትም እንዳሉ አንስተዋል።
በመጨረሻም የሁለቱም ከተማ የሰላምና ፀጥታ መዋቅር ሀላፊዎች በጸጥታው ዙሪያ በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን ሰነድ ተፈራርመዋል ።